መቀመጫቸው አዲስ አበባ ያደረጉ እነዚህ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮችን፤ በጽ/ ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ከሁለት ዓመት በፊት የተፈረመው የሰላም ውል፤ በምሉእነት ባለመተግበሩ የጦርነቱ ተፈናቃዮች አልተመለሱም፣ የትግራይ ችግር ሊፈታ አልቻለም ሲሉ ለልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሪቶርያው የሰላም ውል በምሉእነት እንዲተገበር አምባሳደሮቹ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ተዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪ፤ በመቐለ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የጀርመን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ የፈረንሳይ እና የአውሮጳ ሕብረት አምባሳደሮች ከህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ፤ በኢትዮጵያ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታዉቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ባወጣው መግለጫ፥ የፕሪቶርያ ስምምነት የተፈራረሙ አካላት ዝምታቸው በመስበር በትግራይ አደጋ ላይ ላሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲደርሱ ጥሪ አቅርቧል።
የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ባለመተግበሩ በትግራይ በርካቶች ለአደጋ ተጋልጠዋል ያለው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ህወሓት ግን በክልሉ ያለዉን ችግር ወደጎን በማለት እርስ በርስ ፕሮፖጋንዳ ዉስጥ ተጠምደዋል ሲልም ኮንኗል።
የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
