በትግራይ ክልል የአምፑላንስ እጥረት እንዳለ ተነገረ።

በትግራይ ክልል አገልግሎት ላይ ያሉ አምፑላንሶች ከመቶ እንደማይበልጡ ሰምተናል።

ከጦርነቱ አስቀድሞ በክልሉ ከሶስት መቶ በላይ የህክምና ተሽከርካሪ አምፑላንሶች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ከ100 ያልበለጡ መሆናቸዉንም ሰምተናል።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች እና ህፃናት ጤና ዘርፍ ባለሙያዉ አቶ ገብረሀዋርያ ገብረ ክርስቶስ ባሉት አምቡላንሶች በምጥ ለተያዙ እናቶች በፍጥነት ለመድረስ በክልሉ ያለዉ የነዳጅ እጥረት ፈታኝ እንደሆነባቸዉ ገልፀዋል።

በዚህም እናቶችን ለማዋለድ እና እርዳታ ለመስጠት  በያሉበት የህክምና ባለሙያዎች ለመላክ እየተሞከረ መሆኑን ባለሙያዉ ይገልፃሉ።

በክልሉ ያለዉ የጤና ስርአት አገልግሎት  መፍረስ የነፍሰጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ እንዲህም ወሊድ ሂደት ላይ እክል ሆኖ መቀጠሉ ተነስቷል።

በተለይም እናቶች  የቅድመ ወሊድ ክትትሎች በሚፈለገዉ ልክ  እያደረጉ አይደለም ተብሏል።

ከጦርነቱ በፊት በመንግስት ይሸፈኑ የነበሩ የህክምና ክፍያዎች አሁን ላይ ባለመኖሩ እናቶች ከፍለዉ አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆኑን አቶ ገብረ ሀዋሪያ ገብረክርስቶስ ተናግረዋል።

የአምፑላንስ ÷ የሚድዋይፍሪ ባለሙያዎች እጥረት÷ የስልክ አገልግሎት አለመኖር ለወላድ እናቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል ችግሩም ከአቅማችን በላይ ነዉ ሲሉ ባለሙያዉ ተናግረዋል ።

ክልሉ በነበረበት የጦርነት ሁኔታ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዉድመት ማጋጠሙ ተከትሎ  የመልሶ ግንባታ ስራዉ በተፈለገዉ ልክ እየሄደ እንዳልሆነ ሰምተናል።

የጤና ኬላዎቹን ለማቋቋም ከተለያዩ አጋዥ ተቋማት ጋር በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሞከረ ነዉ ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ ተደርጓል የተባለ ጥናት እንዳመላከተዉ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከጦርነቱ በፊት ከነበረዉ ማሻቀቡን ገልፆ ነበር።

ቁምነገር አየለ

የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *