በማይናማር 7ሺህ በላይ የተለያዩ ዜጎች በተለያዩ ካምፓች ታግተው ይገኛሉ፡፡
በተለያዩ የውጪ የስራ እድሎች ተታለዉ በማይናማር እና በታይላንድ ካምፓች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከማይናማር ወደ ታይላንድ ገበተው ፤ ከታይላንድ ወደ ሃገራቸዉ መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች መንግስት ይድረስልን ሲሉ ለጣያችን ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
እነዚህ ኢትዮጲያውያን፤ በማይናማር እና በታይላንድ ከተያዙበት ካምፕ እስካሁን ባለመውጣታቸው ምክንያት ለተጨማሪ ጉዳቶች እየተዳረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
እስካሁን ከማይናማር ወደ ታይላድ የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ብዛት 138 እንደሆነ ያረጋገጠው በሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በበኩሉ አስፈላጊው ሰነድ ተሟልቶላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ መገለፁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከእነዚህ ካምፖች ለማስወጣት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ከማይናማር መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።
ያነጋገርናቸዉ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደገለፁት ከሆነ አሁንም ቢሆን ችግሮችን በመፍታት ወደ ሀገራችዉ እንዲመለሱ እየተደረገ አይደለም ብለዋል።
ጣቢያችን ይህንን ቅሬታ ይዞ የሚመለከተዉን አካል ለማናገር ሞክሮ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ይዞት በወጣው ዘገባ ከታይላንድ ጋር በምትወሰነው ማይናማር ውስጥ በሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ አሁንም ከ 7 ሺ በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙ ዘግቧል፡፡
እስካሁን በታይላንድ እና ማይናማር ድንበር 1 መቶ ሺ የሚገመቱ ሰዎች በደላሎች እንደተታለሉም ዘገባው አክሏል
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
