የፓኪስታን እና የአፍጋኒስታን የጸጥታ ሃይሎች በቅርቡ በተዘጋው የሁለቱ ሀገራት ዋና ድንበር “ቶርካም” ላይ የተኩስ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን የአፍጋኒስታን አንድ የፀጥታ ሃይል አባል ሲገደል ሁለቱ መቁሰላቸው ተገልጿል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሁለት የፓኪስታን የደህንነት ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት በግጭቱ የጸጥታ ሃይሎቻቸው ቆስለዋል።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው በቅዱሱ የረመዳን ወር የመጀመሪያ የስራ ቀን ነው ያሉት ምንጮቹ ፤ይህ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አፍጋኒስታን ከፓኪስታን ምግቦችን በከፍተኛ ደረጃ የምታስገባበት ነው ብለዋል።
በግጭቱ ምክንያት በሁለቱም ወገን በኩል መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ የጫኑ 5 ሺህ የሚጠጉ የጭነት መኪኖች ድንበሩ ላይ ቆመዋልም ተብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤የአፍጋኒስታን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በገባበት ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ አደጋ በተጋለጡበት እና ግማሽ ያህሉ ህዝብ በሕይወት ለመትረፍ ሰብአዊ እርዳታ በሚጠባበቅበት በዚህ ወቅት ግጭቱ መከሰቱ የበለጠ ሀገሪቱን መቋቋም የማትችልበት ችግር ውስጥ ሊከታት ይችላል ሲል ገልጿል።
ሁለቱም ሀገራት በቅርቡ የሚያዋስናቸውን ቶርክሃም እና በደቡብ ምዕራብ የሚገኘውን ቻማን ድንበር ዘግተዋል።
የፓኪስታን ኬይበር ወረዳ የንግድ እና ኢንዱስትሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዩሳፍ አፍሪዲ፤እስካሁን ድረስ የቶርክሃም መዘጋት ቢያንስ 15 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አስከትሏል፣ ሲሉ ተናግረዋል።
በአፍጋኒስታን የናንጋርሃር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻኪሩላህ ሳፊ በበኩላቸው ፤ የአፍጋኒስታን ነጋዴዎች በድንበሩ መዘጋት የተነሳ በቀን 500 ሺህ ዶላር እያጡ ነው ብለዋል።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በ2024 ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ነበር ሲል አስታውቋል።
ልኡል ወልዴ
የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም
