የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍርካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ303 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአምስት ክልሎች የከርሰምድር ውሃ ጥናት ዲዛንና ቁፋሮ ቁጥጥር ለማካሄድ ከአራት ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት አድርጓል፡፡
የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ( ዶ/ር ኢ/ር) ለከርሰምድር ውሃ ስራ የጥናት ምዕራፍ ዋነኛውና መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ በመተግበር በታቀደው ጊዜ፣ ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ለስራው ፍጥነትና ጥራት የተቋማችንን የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች፣ አማካሪዎችና አመራሮችን ማሳተፍና በቅንጅትና በትብብር መስራትንም ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ዲዛይንና የጉድጓድ ቁፋሮ ቁጥጥር የሚደረገው በ5 ክልሎች ሲሆን በአማራ ክልል ሞጣ መካነ ሰላም አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ አካባቢ፣ በሶማሌ ከልል ጀረር አካባቢ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በላይኛው ብላቴ አካባቢ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወይጦ አካባቢ እንደሆነ ተገልጻል፡፡
ውል የወሰዱት ድርጅቶች ሲጋፒ (SIGAPI)፣ ኤላርድ (ELARD)፣ ኤስጂአይ (SGI) እና ዳር አል-ሀንደሳህ ( Dar Al Handasah) የተባሉ አለምአቀፍ ድርጅቶች መሆናቸውን በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም
