የፍቼ የብዝሀ ህይወት ጂን ባንክ ግንባታ በ2004 አ.ም ቢጀምርም በኮንትራት ዉሎች መቋረጥ ምክንያት ስራዉ ተጓቶ ቆይቷል።
የኢትዩጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዩ የዚህ የተለዋጭ ጂን ባንክ የመልሶ ግንባታ በአንድ አመት ዉስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለኢትዩ ኤፍኤም አስታዉቀዋል ።
ለዚህ ግንባታ መዘግየት ምክንያት ሆነዋል የተባሉትን ሁኔታዎች ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በ2004 ዓ.ም የተጀመሩትን ፕሮጀክቶችን የያዘው ኮንትራክተር ስራውን ሳያስረክብ በመጥፋቱ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ በኮንትራክተሩ ላይ ውሳኔ ቢሰጥም ኮንትራክተሩ ባለመገኘቱ ስራው መጓተቱን ገልፀዋል።
ይህን ተከትሎ በ2014 ዓ.ም ገንዘብ ሚኒስቴርን በማስፈቀድ በድጋሚ ጨረታ ቢወጣም ጨረታውን ካሸነፈው ኮንትራክተር ጋር ውል በመቋረጡ ነዉ ተብሏል።
ተቋሙ ከግብርና ሚኒስቴር ና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ስራውን እንደ አዲስ ለማስጀመር እንደተቻለ ተነግሯል።
አሁን ላይ የፍቼ ጂን ባንክ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ግንባታዉ የተጀመረበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር መለሰ ማርዩ ገልፀውልናል።
ባለፈዉ አመት በዚህ የጂን ባንክ ላይ ምልከታ ያደረገዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፍቼ ብዝሃ ህይወት ጂን ባንክ ተጀምረው የተቋረጡ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲቀጥሉና እንዲጠናቀቁ ሲል አሳስቧል።
የፍቼ ብዝሀ ሕይወት ጂን ባንክ የተለያዩ የአዝርዕትና ሆርቲካልቸር፤ የደንና የግጦሽ የእንስሳት ብዝሀ ሕይወት ሀብትን ለመጠበቅ ከሚሰሩ ማዕከላት አንዱ ነዉ ተብሏል።
ቁምነገር አየለ
መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም
