3ኛው ዙር የአፍሪካን ሮቦቲክስ ሻምፒየንሺፕ ውድድር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።
ውድድሩ ከዛሬ መጋቢት 4 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በዚሁ በሳይንስ ሙዚየም እንደሚቀጥል ተነግሯል።
በዚህ ውድድር የመጀመሪያ ደረጃ፤ የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተወዳደሩ ሲሆን በዲዛይኒንግ፤ በኢንጂነሪንግና በአውቶነመስ ኮዲንግ ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ሮቦቲክስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይክረም መኮንን ፤ለፍጻሜ የሚበቁ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለምአቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ላለፉት 15 ዓመታት የነገዎቹን ኢንጂነሮችና ፕሮግራመሮች የመፍጠር ራዕይ ሰንቆ ሲሰራ የቆየው ማዕከሉ፤ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በዓለምአቀፍ የሮቦቲክስ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉና ዓለምአቀፍ ልምድና ተሞክሮ እንዲቀምሱ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው፤ውድድሩ አሁን አለማችን በደረሰችበት ጊዜ ይህ ዘርፍ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ፣ ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ ለማብቃት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የነገ የኢትዮጵያን ብሎም የዓለም ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊዎች ላይ የጀመረው ስራ የሚያስመሰግን በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
ባለፈው ዓመት በቻይና ሻንጋይ በተካሄደው ኢንጆይ ኤ.አይ ዓለምአቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ 21 ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ሀገራቸውን ወክለው የተወዳደሩ ሲሆን፤ በውድድሩ ከተሳተፉ 27 የዓለም አገራት 3ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ልኡል ወልዴ
መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
