35ኛ ቀኑን በያዘዉ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር 7መቶ43 ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ከየካቲት 01 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሰይፉ በኢቢኤስ ዩቲዩብ ቻናል እየተደረገ በሚገኘዉ የቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰብያ መርሃግብር ላይ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
መቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በአዲስ አበባ እና በክልል የጀመረዉን ስራዉን ለማጠናቀቅ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
እየተካሄደ ባለው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እየተገነቡ ለሚገኙ ህንጻዎች ሴራሚክስ፣ የኤሌትሪክ ዕቃዎች፣ የውኃ ቧንቧዎች ፣ የመፀዳጃ ቤት ዕቃዎች እና የመሳሰሉትን መግዣ የሚውል እንደሆነ ተገልጿል።
መቄዶንያ በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ አድዋ፣ ባህርዳር እና ሌሎችንም ጨምሮ በአጠቃላይ በ44 ከተሞች ቅርንጫፍ በመክፈት ስራውን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
በቀጣይም በወሊሶ፣ ሱልልታ፣ ሰበታ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ጂግጂጋ፣ እና በሌሎች ከተሞች ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታዉቋል፡፡
መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብ እና መፀዳዳት የማይችሉ የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማንን በማገዝ ላይ የሚገኝ ተቋም ነዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም
