ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በፍጥነት ተግባራዊ ይደረግ የተባለውን የተኩስ አቁም ስምምነት አልቀበልም ብለው ነገር ግን የዩክሬንን የኃይል ማመንጫዎች ላለምታት ቃል ገቡ።
ፑቲን ይህ ያሉት ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ልውውጥ በኋላ ነው።
የሩሲያው መሪ ለአንድ ወር የሚቆይ የተባለውን ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ውድቅ አድርገውታል። ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት በሳዑዲ አራቢያ ያረቀቁት ነው።
ፑቲን እንዳሉት ይህ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ሊሠራ የሚችለው የውጭ ኃይሎች ለዩክሬን የሚያደርጉት የመሣሪያ እና የመረጃ አቅርቦት ካቆሙ ብቻ ነው።
የዩክሬን አጋር የሆኑ አውሮፓውያኑ ሀገራት ከዚህ ቀደም ይህን የፑቲን ቅደመ ሁኔታ እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር።
በሳዑዲ መዲና ጅዳ በዩክሬን ጉዳይ የሚደረገው ንግግር እንደሚቀጥል በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ልዑክ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ከፑቲን ጋር የነበራቸው የስልክ ልውውጥ “በጣም መልካም እና ውጤታማ” እንደነበር ፅፈው ለጊዜው የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ከስምምነት እንደተደረሰ፤ በቀጣይ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ውይይት እንደሚቀጥል ፅፈዋል።
80 በመቶ የሚሆኑት የዩክሬን የኃይል ማመንጫ መሠረተ-ልማቶች በሩሲያ የቦምብ ጥቃቶች መውደማቸው ዜሌንስኪ ባለፈው መስከረም መናገራቸው ይታወሳል።
መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም
