በክልሉ ያለዉ አለመረጋጋት መጠነ ሰፊ የማህበራዊ ቀዉስ ተጋላጭነት እንዲኖር እያደረገ ነዉ ተብሏል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ የሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያ እና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ፀጋዉ አንፃራዊ ሰላም ይገኝባቸዋል በተባሉ ባህር ዳር÷ ጎንደር ÷ ደሴ÷ እንዲሁም ዋና ዋና የዞን ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር እንዳለ ተናግረዋል።
በነዚህ ሶስት ከተሞች ላይም ሴተኛ አዳሪነት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ሰምተናል።
ኢትዩ ኤፍአኤም ያነጋገራቸዉ የቢሮዉ ዳይሬክተር እንደገለፁት ይሄን ህይወት እየተቀላቀሉ ያሉ ሴቶች ቁጥር መጨመሩን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
ባለሙያዉ በክልሉ በባለፈዉ አመት 18 ሺህ 264 ያህል ሴቶች እንዳሉ መረጃዎች የጠቆሙ ሲሆን በዚህ አመት የተሰበሰበዉ መረጃ 54 ሺህ 950 መድረሳቸዉን አሳይቷል ብለዋል።
በተመሳሳይ የዜጎች መፈናቀልን ተከትሎ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና በልመና እየተዳደሩ የሚገኙ አረጋዉያን እና ወጣቶች ቁጥር ጨምሮ መስተዋሉን ተናግረዋል።
ግጭቱ ባስከተለው ስጋት የዜጎች ኢኮኖሚ ስርአት መፍረስ ÷ ፆታዊ ጥቃቶች መበራከት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
እነዚህ ከተሞች ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች እየተቀበሉ ሲሆን በአካባቢው ራስን ለማኖር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ባለመኖሩ ዜጎች እነዚህን አማራጭ እያደረጉ ነዉ ተብሏል።
የክልሉ ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ የተባለ እንቅሰቃሴ ማድረግ እንደተሳነዉ ባለሙያዉ ገልፀዋል።
በባለፉት ስድስት ወራት እንኳን 6 ወረዳዎች ብቻ በመድረስ ያሉ ኘሮግራሞችን ለመተግበር እንደተቻለ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከዩኒሴፍ ጋር በመሆን ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ የተናገሩት ባለሙያዉ ለሌሎች አጋር አካላት ትብብር እንደሚያስፈልጋቸዉ ገልፀዋል።
ቁምነገር አየለ
መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም
