በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም የጎዳና ላይ ገጽታንና ደህንነትን ለመጠበቅ በሚል ባለቤት አልባ የጎዳና ላይ ውሾችን ወደ መጠለያ የማስገባት ሥራ ሊጀመር መሆኑን አስታወቀ፤ ጎዳና ላይ ያሉ ውሾችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማምከን ሥራ እንደሚሠራም ገልጿል።
ባለቤት አልባ የጎዳና ላይ ውሾችን የመጠለያ ማዕከል አዘጋጅቶ ወደዚያ ለማስገባት የሚያስችል አዲስ የአሠራር ደንብ ተዘጋጅቷል ሲሉ የአስተዳደሩ የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ የሺ ዳኜ እንደገለጹለት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በድረገጹ አስነብቧል።
ደንቡ በረቂቅ ደረጃ ያለ መሆኑን እና በቅርቡም ወደ ሥራ ይገባል ሲሉ ሃላፊው ነግረውኛል ያለው ጋዜጣው በአሠራር ደንቡ መሠረት ባለቤት አልባ የጎዳና ላይ ውሾችን ወደ መጠለያ ለማስገባት መጀመሪያ የውሻ ባለቤትነት ምዝገባ ይካሄዳል ማለታቸውንም አካቷል።
ውሻ አለኝ የሚል ማንኛውም ሰው ምዝገባ ማድረግ አለበት፤ የውሻ ባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ሰነድ ይሰጠዋል ማለታቸውንም አስታውቋል።
በባለቤትነት ደንቡ መሠረት ማንኛውም ሰው “ውሻውን ይቆጣጠራል፣ ተገቢውን አያያዝ ያደርጋል፣ በየዓመቱ ክትባት ማስደረግም ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ማሳሰባቸውንም አስታውቋል።
አዲስ ደንብና መመሪያ ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት ባለቤታቸው የማይታወቅ የጎዳና ላይ ውሾች በብዛት በመታየታቸው ምክንያት ነው፤ በቀጣይ የጎዳና ላይ ውሾች ቁጥር እንዳይበራከት ዘመናዊ በሆነ የማምከን አሠራር እንዳይራቡ ይደረጋል ማለታቸውንም አካቷል።
መጀመሪያ አሁን ላይ ያሉት ወደ መጠለያ እንዲገቡ፤ የገቡትም እንዳይራቡ ይደረጋል ማለታቸውን አስታውቋል።
መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም
