በሚያንማር ርዕደ መሬት ከ2ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥትም የአንድ ሳምንት ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።
በ7.7 ማግኒትዩድ የተለካው ርዕደ መሬት የተነሳበትን ሰዓት ለማስታወስ የኅሊና ፀሎትም ይደረጋል።
በርዕደ መሬቱ ሳቢያ የተጎዱት ሰዎች ከ4,000 በላይ መሆናቸው ተገልጿል።
በሚያንማር ጎረቤት ታይላንድ በርዕደ መሬቱ ንዝረት 20 ሰዎች ሞተዋል።
በባንኮክ ሕንጻዎች በመሰነጣጠቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል።
በሁለቱም አገራት ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ሙከራው ቢቀጥልም ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ተስፋው እየተመናመነ መጥቷል።
ርዕደ መሬቱ ከተነሳ 72 ሰዓታት በማለፋቸው ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ዕድሉ ጠቧል።
ለአምስት ቀናት የሚያንማር ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ወታደራዊ መንግሥቱ ገልጿል።
ዜጎች በያሉበት ሆነው ለተጎጂዎች የኅሊና ፀሎት ያደርሳሉ።
ወታደራዊ መንግሥቱ ሩሲያ፣ ቻይና እና አሜሪካን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እርዳታ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተራድኦ ድርጅቶች እንዳሉት በቀጣይ የሚኖረው ሥራ ከባድ ይሆናል። የተለያዩ በሽታዎች ሊነሱ የሚችሉ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት ውድመት የእርዳታ ሥራውን የሚያስተጓጉልም ይሆናል።
ቢቢሲ በርሚዝ የተመለከታቸው አካባቢዎች የእርዳታ ሥራ በሁሉም ሥፍራ አለመጀመሩን ያሳያሉ።
በይፋ የሟቾች ቁጥር 2,000 ይደርሳል ቢባልም ወታደራዊው መንግሥት የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር በማሳነስ ይታወቃል።
መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም
