የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “በየሁለት ሳምንት” ልዩነት፤ “መደበኛ” እና “ተከታታይ” የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ” ሊጀምር እንደሆነ አስታወቀ። “የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጪ ምንዛሬ ስርዓት ግብ ለማሳካት” የታቀደ ነው የተባለለት ጨረታ፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 23፤ 2017 ይጀመራል።
በዛሬው ጨረታ 50 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ የቀረበ ሲሆን፤ ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡ ብሔራዊ ባንክ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል።
በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጪ ምንዛሬ ተመን ስርዓት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ከተደረገ ወዲህ ብሔራዊ ባንክ ሁለት ጊዜ ዶላር ለባንኮች በጨረታ ሸጧል።ጨረታው ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ የገለጸው ብሔራዊ ባንክ፤ ውጤቱ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።
ይህ ጨረታ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በባንኮች እና በደንበኞቻቸው ድርድር እንዲወሰን ከተደረገ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው። ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ማከፋፈል የጀመረው፤ በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ ከተደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጥ በኋላ ነው።
የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ማሻሻያው፤ ብሔራዊ ባንክን በግብይቱ ውስጥ ከነበረው ጉልህ ሚና ያስወጣ ነው። ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚታወቅበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ “መሰረታዊ በሚባል ደረጃ እየተቃለለ” መምጣቱን እና “የውጭ ምንዛሬ ፍሰት” እየጨመረ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ተናግረዋል ሲል ኢትዮጲያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም
