ጃፓን በግጭት በተጠቃው ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል የአገልግሎት አሰጣጥና የህግ ማስከበር ስራን ለማጣናከር እገዛ ታደርጋለች ተባለ፡፡
የጃፓን መንግስት የኢትዮጵያን ሰላም እና የመልሶ ማቋቋም ጥረት ለማገዝ በሚደረገው ጥረት ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተነግሯል
ጃፓን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ቁልፍ አጋር ሆኖ ቆይታለች፡፡
ከሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በኋላ የአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች እያደረጉ ያሉትን የመልሶ ግንባታ ጥረት ለማገዝ ሶስት ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጓን ኢንባሲው ለኢትዩ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አሳውቋል፡፡
አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጃፓን ለዘላቂ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
‹‹ የጃፓን መንግስት የሰዎች ህይወት ከቅግጭቱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ በፍጥነት ለመመለስ የሚያግዝ ድጋፍ አድርጓል፡፡የክልሎች የስራ ኃላፊዎች የሰዎችን ኑሮ መልሶ ለማቋቋም ከፍ ያለ ተነሳሽነትና ጥረት ማሳየታቸውን አደንቃለሁ ብለዋል፡፡
በጃፓን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ከሚሰሩ ነገሮች መካከል መንግስታዊ መዋቅሮችን ወደ ነበሩበት መመለስ አንዱ ነው፡፡ 190 መንግስታዊና የፍትህ ቢሮዎች፣ 64 ትምህርት ቤቶች እና 22 የጤና ተቋማትና ተጠግነው ስራ ላይ እንዲውሉ ጥረት ተደርጓል፡፡
ድጋፉ የሰዎችን በተለይም የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ህይወት እንደሚያሻሻል ይታመናል፡፡ ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ተፈናቃዮችን እንደሚያግዝም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ የጃፓንን ድጋፍ አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡ ‹‹ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና የመልሶ ግንባታውን ሂደት በማገዝ ረገድ የጃፓን መንግስት የማይተካ ሚና አለው›› ብለዋል፡፡
ጃፓን የክልሎችን የመልሶ ማቋቋ ቢሮዎች፣ የፖሊስ ኃይል እና የወረዳ አስተዳደሮችን የስራ ሂደት ለማጠናከር የሚያግዙ 12 የሞተር ብስክሌቶችን እና ሶስት መኪኖች ገዝታለች፡፡
የሞተር ብስክሌቶቹ ይፋዊ ርክክብ የአማራ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ(ዶ/ር) እና የአፋር ክልል የመልሶ ግንባታእና ማቋቋሚያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን ሞሃመድ በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከናውኗል፡፡
መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም
