ግለሰቦቹ ሆን ብለው በመዘጋጀት በርከት ያለ ገንዘብ የያዙ ለማስመሰል በሁለት መቶ ብሮች የተጠቀለሉ ባለ አስር ብር ኖቶችን በመያዝ የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሰዎች ላይ የሚያዩትን ጌጣ ጌጥ አታለው በገንዘቡ ለመቀየር ካልሆነም የበለጠ ገንዘብ የሚያገኙበትን ዘዴ ይፈጥራሉ፤ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚፈፀሙት የወንጀል ድርጊት መሆኑን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡
ሚያዚያ 8 ቀን 2017 ዓ/ም በተመሳሳይ የወንጀል አፈጻፀም ሙከራ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ዳንኤል ታደሰና ታዬ ዋቅጅራ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ከላይና ከታች በባለ 200 ብር ኖት የተሸፈነና መሀሉ በባለ 10 የብር ኖት ጥቅልል የተዘጋጀ ገንዘብ በመያዝ በሆስፒታሉ እናቷን እያስታመመች የነበረችና መድኃኒት ለመግዛት የወጣችን ግለሰብ በማግባባት የታወቁ ስፔሻሊስት ዶክተሮች መሆናቸውን በመግለፅ ለማጭበርበሪያነት የያዙትን ጥቅልል ብር ካሳዩኋት በኋላ በ10 ብር እንዲቀይሯት ይጠይቋታል ።
ሁኔታቸው ያላማራት የግል ተበዳይም የግለሰቦቹን ሁኔታ በመጠራጠር ጩኸት ታሰማለች ግለሰቦቹም ወዲያውኑ በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላሉ፡፡
በምርመራው ለማረጋገጥ እንደተቻለው የግል ተበዳይ በፍጥነት ነቅታባቸው ባይያዙ ወደ ባንክ ወይም ወደ ኤ.ቲ.ኤም ይዘዋት በመሄድ ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ገንዘብ ሊያስወጧት እንደነበርም ፖሊስ ገልጿል።
የግል ተበዳይ ለፖሊስ በሠጠችው ጥቆማ መነሻነት ምርመራው የቀጠለ ሲሆን ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ የወንጀል አፈፃፀም የጣት ቀለበት የተወሰደባት ሌላ ግለሰብ መረጃ ለመስጠት ወደ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደመጣች ታውቋል፡፡
ሌሎች ተመሣሣይ ወንጀል ተፈፀሞብናል የሚሉ ለየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ መረጃ መስጠት እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል።
ወንጀል ፈጻሚዎች የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ወንጀል ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ በማንኛውም እንቅስቃሴያችን ትኩረት ሊለየን አይገባም ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
