የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለቀረበበት የስም ማጥፋት ውንጀላ ምላሽ ሰጠ፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለፈፀመብን ስም ማጥፋት ማስተካከያ ያድርግ ሲሉ ሶስት ማህበራት በጋራ መግለጫ አውጥተውበታል፡፡
ለዚህ ምላሽ የሠጠው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ “በተሰጠን ሃላፊነት ነው የሰራነው ብሎናል ፡፡
ለህጋዊነታቸሁ ማረጋገጫ አምጡ ብለናቸው ምንም ምላሽ ሳይሰጡ በዛው ቀርተዋል ሲልም ቢሮው ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ላይ መግለጫን ያወጡት የኢትዮጵያ የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማህበር፣ የውጭ ኦዲተሮች ማህበር እና አካውንቲንግ ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡
የሙያ ማህበራቱ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በንግድ ስራ ምሩቃን ማህበር ግቢ ውስጥ በሰጡት መግለጫ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ያለስልጣኑ ጣልቃ በመግባት የስም ማጥፋት ፈፅሞብናል ብለዋል፡፡
ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ይህን የማደርገው በታክስ አስተዳደር አዋጅ በተሰጠኝ ስልጣን መሰረት ነው ሲል ለዚህ ምላሹን ሰጥቷል ፡፡
ምንም እንኳን ቢሮው ይህን የማድረግ ስልጣን አለኝ ቢልም ሶስቱ የሙያ ማህበራት ግን የቢሮውን ተግባርን በመቃወም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
ማህበራቱ በመግለጫቸው ቢሮው ያለው ስልጣን ለኢትዮጵያ የሂሳብ እና የኦዲት ቦርድ ማቅረብና ማስወሰን እንጂ፣ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በራሱ ገምግሞና ውሳኔ ሰጥቶ በሚዲያ ማሰራጨቱ በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በተጨማሪም “የጥፋተኝነት ውሳኔ ባልተሰጠበት ሁኔታ ይህን ማድረጉ ተገቢ አይደለም፤ በሙያውና ሙያተኞቹ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ተፈፅሟል ብለዋል፡፡
ባለሙያዎቻችን እንደሌባ እንዲታዩ፣ በሃገርና በመንግስት ላይ ክህደት እንደፈጸሙ፣ በየሄዱበት እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ ተግባር ነው” በማለትም የቢሮውን ድርጊት በመቃወም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የጠየቅናቸው የአዲሰ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ በበኩላቸው ቢሯችን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሰራነውን ስራ ይፋ አደረግን እንጂ የስም ማጥፋት ውስጥ አልገባንም ብለዋል፡፡
ቅሬታውን ያቀረቡት ሶስቱ ማህበራት ከቢሮው ለመነጋገር መድረክ ይፈጠርልን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ሰውነት “በገቢዎች ቢሮው በኩል ለመነጋገር ፍቃደኛ ነበርን፤ በቅድሚያ ግን ለህጋዊነታቸሁ ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ አምጡ ብለናቸው በዚያው ጠፍተዋል ሲሉ ነግረውናል፡፡
አንዳቸውም ህጋዊ ሰነዱን ለማቅረብ ፍቃደኛ አልሆኑም፣ እየጠበቅናቸው ነው” በማለት ምላሽ ሰጠተዋል፡፡
እንደ ማህበር ህጋዊ ዕውቅና ያላችሁ ስለመሆናቸሁ ከሚያረጋግጥ አካል ማረጋገጫ፣ እንዲሁም በስራቸሁ ያሉ ኦዲተሮችም ሆኑ የሂሳብ ባለሙያዎች ህጋዊነት አርጋግጡልን ብንላቸውም ሽሹ ነው ያሉት፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለውም ህጋዊነታቸው ላይ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡
ህጉን የማያውቁት ከሆነ ማንበብ ነው፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 48 በግልጽ አስቀመጧል፡፡ ቢሮው ግቢ የመሰወርና የማሳነስ ተግባር ተፈጽሞ ከሆነ አረጋግጦ ለኢትዮጵያ የሂሳብ ባለሙያዎች ቦርድ እርምጃ እንዲወሰድ ይፅፋል (ያቀርባል) በማለት በግልጽ ያስቀመጠው ነው ሲሉ የማህበራቱን ውንጀላ አጣጥለዋል፡፡
አዲስዓለም አበበ
ሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
