በጋዛ የፀረ-ሃማስ ተቃውሞ እየተበራከተ መጥቷል ተባለ

በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ፍልስጤማውያን ለ20 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ግዛቱን ሲመራ በነበረው በታጣቂው ቡድን ላይ ግልጽ የሆነ እምቢተኝነትን እየገለጹ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

በርካቶች ለግዛቷ ድህነት እና በአስከፊ ቀውስ እንድትዘፍ ያደረገው ሀማስ ነው ሲሉ ተጠያቄ አድርገዋል፡፡

የጋዛ ጠበቃ እና የቀድሞ የፖለቲካ እስረኛ የሆኑት ሀማስን ለረጅም ጊዜ ሲተቹ የነበሩት ሙመን አል ናቱር “አለም በጋዛ ሰርጥ ባለው ሁኔታ ተታልሏል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“አለም ‹ ጋዛ ሃማስ› ‹ሃማስ ጋዛ › ነው ብሎ ያስባል። እኛ ሃማስን አልመረጥንም፤ አሁን ሃማስ ጋዛን ለመግዛት እና እጣ ፈንታችንን ከራሱ ጋር ለማያያዝ ቆርጦ ተነስቷል። ሃማስ ማፈግፈግ አለበት” ብለዋል፡፡

በጋዛ ይህን መሰል ነገር መናገር እጅግ አደገኛ ነው የሚሉት ሙመን ። ሃማስ ተቃውሞን በፍፁም ችሎ አያውቅም ሲሉ ያክላሉ።

ጠበቃው በመጋቢት መጨረሻ ላይ ለዋሽንግተን ፖስት በላኩት ጽሑፍ ሃማስን መደገፍ ለፍልስጤም ሞት እንጂ የፍልስጤም ነፃነት አይደለም ሲል ጽፈዋል።

በሌላ ዜና የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ሀማስ ጋዛ ውስጥ የያዛቸውን ታጋቾች በሙሉ እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡

አባስ፣ ሀማስ ታጋቾቹን ይዞ መቆየቱ እስራኤል በፍልስጤም ጥቃቷን እንድትቀጥል ሰበብ ሆኗታል ብለዋል።

አባስ ጥያቄውን ባቀረቡበት በዛሬው እለት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባካሄደችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገልድለዋል።

አባስ ዛሬ በፍልስጤም አስተዳደር መቀመጫ ራማላህ ውስጥ በተካሄደ ውይይት ላይ «ዋጋ ከሚከፍሉት መካከል አንዱ እኔ ነኝ ፣ህዝባችንም ዋጋ እየከፈለ ነው »ካሉ በኋላ ሰዎቹን አስረክቡ ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ጥቃት ማካሄዷን የቀጠለችው ከሀማስ ጋር የደረሰችበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ከአምስት ሳምንት በፊት ካፈረሰች በኋላ ነው።

በተኩስ አቁሙ ወቅት ከጋዛ 33 ታጋቾች ሲለቀቁ ከእስራኤል ወህኒ ቤቶች ደግሞ 1800 ፍልስጤማውያን ተፈተው ነበር።

አባስና የፍልስጤም አስተዳደር ብዙውን ጊዜ ሀማስ የፍልስጤማውያንን አንድነት ዝቅ አድርጎ ይመለከታል ሲሉ ይከሳሉ።

ሀማስ በበኩሉ አባስንና አስተዳደራቸውን ከእስራኤል ጋር እና በዌስትባንክ በሚካሄደው አፈና በመተባበር ይተቻቸዋል።

ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *