ኩባንያው የ10 በመቶ የአክስዮን ድርሻውን ወደ ገበያው ካቀረበ በኋላ 10.7 ሚሊየን አክስዮን መሸጡን አስታውቋል።
ጥቅምት 7 የጀመረው የአክስዮን ሽያጭ 47ሺህ 3መቶ 77 ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ተሳትፈውበታል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ጥቅምት 7 የተጀመረው የአክስዮን ሽያጭ ታህሳስ 25 ያበቃ ቢሆንም በተለያዩ ጥያቄዎች መሰረት እስከ የካቲት 7 ድረስ ተራዝሞ እንደነበር ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ለ1መቶ21 ቀናት ሲሸጥ የነበረው አክስዮን 3.2 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር የተከፈለበት መሆኑንም አንስተዋል።
ገንዘቡም ዝግ በሆነ አካውንት መቀመጡን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ከጥቅምት 7 እስከ ታህሳስ 25 ቀን ድረስ 8.78 ሚሊየን አክስዮን ተሽጧል።
በተራዘመው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 1.87 ሚሊየን አክሲዮን መሸጡን ነው የገለፁት።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የአክስዮን ሽያጩ በመንግስት ፍቃድ ለሁለተኛ ዙር እንደሚቀጥል ገልፀው፤ ቀጣይ የሚኖረው ሽያጭ ቀድመው አክስዮኑን በገዙ ባለሀብቶች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከ6 ወራት በፊት የ10 በመቶ ድርሻውን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ለመሸጥ ለገበያ ማቅረቡ ይታወሳል።
በወቅቱም ዝቅተኛው የአክስዮን መጠን 33 ፤ ከፍተኛው ደግሞ 3ሺህ3መቶ 33 ነበር።
እስከዳር ግርማ
ሚያዚያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም
