በሩሲያ ኩርስክ የዩክሬን ኃይሎች ሽንፈት ላይ የተሳተፉትን የኮሪያ ተዋጊዎች ጀግንነትን ህዝባችን ፈፅሞ አይረሳውም ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
“የኮሪያ ወታደሮች ሩሲያን እንደ ሀገራቸው በመቁጠር ሀገራችንን ለመከላከል ከጦር ኃይላችን ጎን ለጎን በመቆም ያሳዩትን ጀንነትና ወዳጅነት እናከብራለን” ሲሉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
የኮሪያ ወታደሮች ሃላፊነታቸውን በክብርና በጀግንነት በመወጣት ዘላለማዊ ታላቅነት ተጎናፅፈዋል ሲሉ ፑቲን አጽንኦት ሰጥተዋል ።
“የኮሪያ ወዳጆቻችን በትብብር፣ በፍትህ እና በእውነተኛ የወዳጅነት ስሜት በመነጨ መልኩ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ይህንን በእጅጉ እናደንቃለን፤ እንዲሁም የሀገሪቷን መሪ ክቡር ኪም ጆንግ-ኡን፣ መላው አመራርቸው እና የሰሜን ኮሪያን ህዝብ ከልብ እናመሰግናለን” ብለዋል ሲል ስፑትኒክ ዘግቧል ።
በሌላ ዜና ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ዩክሬንን የሚዋጉ ወታደሮችን መላኳን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጣለች፡፡
በመንግሥታዊው የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ላይ አገሪቱ ጦር ባሠራጨው ዘገባ ወታደሮቹ በመሪው ኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ የኩርስክን ክልል “ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲያወጡ” ረድተዋል ሲል ገልጿል።
የፒዮንግያንግ ይህንን ያሳወቀችው የሩሲያ አዛዥ ቫለሪ ጌራሲሞቭ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን “ጀግንነት” ካደነቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን፣ ይህም ሞስኮ ተሳትፏቸውን በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳወቀችበት ሆኗል።
ከሰሜን ኮሪያ ከተላኩት 11 ሺህ ወታደሮች መካከል ቢያንስ አንድ ሺህ ያህሉ በሦስት ወራት ውስጥ መገደላቸውን እንደሚያምኑ ቀደም ሲል የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሄራሲሞቭም አክለውም ሞስኮ የኩርስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ መልሳ መቆጣጠሯን ተናግረዋል። ይህ ግን በዩክሬን ውድቅ ተደርጓል።
ለመግለጫው ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ጦርነቱን በማስቀጠሏ ኃላፊነቱን መሸከም አለባት ብላለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሚያዚያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም
