የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሩሲያ ጦርነቱን ለማቆም ያላትን ቁርጠኝነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ማሳየት አለባት ብለዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፤ሩሲያ ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም ተግባራዊ በማድረግ ፈቃደኛነቷን ካሳየች ኪቭ “በምንም ዓይነት መልኩ” የሰላም ንግግሮችን ለመጀመር መዘጋጀቷን አስታዉቀዋል፡፡
ዘሌንስኪ ከትራምፕ ጋር አደረግኩት ባሉት ውይይት የጦር ሜዳው ሁኔታ መገምገሙን እና የ 30 ቀናት የተኩስ አቁም በአስቸኳይ እንዲጀመር ሀሳብ መቅረቡን አንስተዉ፤ ሩሲያ ይህንን ሀሳብ እንድትደግፍ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
ዩክሬን ለዲፕሎማሲያዊ ንግግር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ዩክሬን በማንኛውም መልኩ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለሁ፤ይህ የሚሆነዉ ግን ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም በመጀመር ጦርነቱን ለማስቆም ያላትን ቁርጠኝነት ካሳየች ብቻ ነዉ ብለዋል ፡፡
የዩክሬኑ መሪ አክለውም ትራምፕ የተኩስ ማቆም ሃሳብን እንደሚደግፉ እና ጦርነቱን እንዲያበቃ ለመርዳት ያላቸውን ፍላጎት አረጋግጠዉልኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ግንቦት 1ቀን 2017 ዓ.ም
