በኢትዮጵያ የወተት ገበያ እንቅስቃሴ፣ በህጋዊ ሂደት አልፎ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ የሚውለው 5 በመቶ ገደማ ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእንሰሳት ተዋፅዖና አልሚ ምግቦች ኢንስፔክሽን ዴስክ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ 95 በመቶው የወተት ሽያጭ ሂደት ህጋዊ መስመርን ያልተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
ወተት ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚፈልጉ ምርቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን የገለፁት አቶ መሐመድ “ማንኛውም ሰው እንደፈለገ ወተት እያዞረ መሸጥ አይችልም” ብለዋል። ነገር ግን ይህ ግንዛቤ በማሕበረሰቡ ዘንድ እንደሌለ ነው የጠቀሱት።
የወተት ምርትና ሽያጭ ከሚያስፈልገው ከፍተኛ ጥንቃቄ አንፃር በጀሪካንና በሌሎችም ባልተፈቀዱ ዕቃዎች ማጓጓዝ ጥራቱን ከማጓደል ባሻገር ለበሽታ አምጪ ተዋህስያን የሚያጋልጥ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የወተት ጥራትን ለማስጠበቅ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት የዴስክ ኃላፊው፣ ህጋዊ ሂደቱን በተመለከተ ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አዲስዓለም አበበ
ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም
