ከዚህ በፊት በመንግስት ብቻ ይገነቡ የነበሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን በግለሰቦች እየተገነቡ ነው ተባለ

ከዚህ በፊት በመንግስት ብቻ ይገነቡ የነበሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን በግለሰቦች እየተገነቡ መሆናቸውን ያሳወቀው
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዳንኤል ኦላኒ በኢትዮጵያ 28 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ፓርኮች በግሉ ዘርፍ የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህም የሪፎርሙ ትሩፋት ነው ሲሉ አክለዋል።

የሚኒስትሩ አማካሪ ይህን ያሉት 7ኛው አግሮፉድ እና ፕላስትፕሪንትፓክ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይን አስመልክቶ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

ከሰኔ 12-14 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ይካሄዳልየተባለው አውደ ርዕዩ በጀርመኑ ፌትሬድ መሴ እና በኢትዮጵያ አጋሩ ፕራና ኢቨንትስ አዘጋጅነት በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ14 ሃገራት የተውጣጡ ከ140 በላይ አቅራቢዎች ለኢትዮጵያ ገበያ ተብለው የተዘጋጁ ምርቶችን ያቀርባሉ ተብሏል።

የኢንዱስትሪ ሚ/ር ከሁነቱ አጋሮች መካከል አንዱ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚኒስትሩ አማካሪ ስለሁነቱ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው በኢትዮጵያ ከሚገኙ 28 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ስምንቱ ፓርኮች በግሉ ዘርፍ የተገነቡ መሆናቸው የገለፁት። ይህም የግሉ ዘርፍ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እንዲሰማራ ማበረታቻ ከተደረገ ወዲህ የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም መንግስት የመሰረተ ልማቱን ወጪ፣ የመሬት አቅርቦት፣ የማዘጋጃ አገልግሎትና አጠቃላይ የግንባታውን ወጪ ይሸፍን ነበር ሲሉ አቶ ዳንኤል አስታውሰዋል።

ፓርኮቹ ተጨማሪ መሬት እየጠየቁ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እስከ 2ሺ ባለሃብቶቸን መሳብ የሚችል መሬት ተዘጋጅቷል ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ካሉት 28 ፓርኮች ውስጥ አራቱ ምግብን መሰረት ያደረጉ የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ብለዋል። ከአራቱ ኢንዱስትሩ ፓርኮች ደግሞ 3ቱ ወደ ስራ የገቡ መሆናችውን ገልፀዋል።

አዲስዓለም አበበ

ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *