ከዚህ በፊት ከዉጭ ይገቡ የነበሩ የህክምና መገልገያዎችን በአገር ዉስጥ ማምረት መጀመሩን አገልግሎቱ አስታዉቋል፡፡
ጓንት የሚያመርቱ ሁለት አምራቾች በአገር ዉስጥ መኖራቸዉን አንስተዉ፤ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ የጓንት አቅርቦት በአገር ዉስጥ መሸፈኑን የገለጹት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ናቸዉ፡፡
ድሬዳዋ ላይ የተከፈተ የስሪንጅ ማምረቻ መኖሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ስሪንጅም ከዉጭ ማስገባት ካቆምን አንድ ዓመት አልፎናል ብለዋል፡፡
እንደ ስኳር፣ ግፊት ያሉ መድሃኒቶችም በአገር ዉስጥ መመረት መጀመራቸዉን አንስተዉ፤ 60 በመቶ የሚሆነዉን መድሃኒት በአገር ዉስጥ ለመተካት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት የአገር ዉስጥ መድሃኒት አቅርቦት 8 በመቶ ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ወደ 40 በመቶ መድረሱን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዓመት በአገር ዉስጥ አምራቾች የቀረቡ መድሃኒቶች ቁጥር 97 መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ጥሬ ዕቃ ለማስገባት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ፤ የአገር ዉስጥ አምራቾች በተሻለ ሁኔታ እያመረቱ ነዉ ብለዋል፡፡
ከአገር ዉስጥ አምራቾች ጋር የ11 ቢሊየን ብር ዉል መታሰሩን አንስተዉ፤ እስከ 7 ዓመት በሚደርስ ስምምነት መድሃኒትም ሆነ የህክምና መገልገያዎችን ማምረት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም
