ወደ ሞስኮ ያቀኑት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የሚያደርጉት ውይይት መሰረታዊ እንደሆነ ገልጸው “በተለመዱ ተግዳሮቶች እና ስጋቶች” ላይ ያተኩራል ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ ተወካይ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አውግዘው አሜሪካ በዚህም “አዙሪቱ የማያልቅ” ሁኔታን ከፍታለች ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፑቲን ጋር የሚገናኙ ከሆነ ጠንካራ የቃላት ድጋፍ ሊቸራቸው እንደሚችል ቢታመንም ከሩሲያ ወታደራዊ እርዳታ የማይመስል ነው ተብሏል።
ለዚህም ምክንያቱ ሩሲያ ትኩረቷ ከዩክሬን ጋር የምታደርገው ጦርነት መሆኑ ነው።
ምንም እንኳን ሩሲያ እና ኢራን የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ቢኖራቸው ይህ የመከላከያ ስምምነት አይደለም።
ይህም ለኢራን ወታደራዊ ድጋፍ እንድትሰጥ የሚያስገድድ አይደለም።
ባለፈው ሳምንት ኢራን ከሩሲያ ወታደራዊ እርዳታ አለመጠየቋን ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናግረው ነበር። ፑቲን ከኢራን እና ከእስራኤል ጋር ጥሩ ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን፤ ከዶናልድ ትራምፕ ጋርም ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት አላቸው።
ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም
