በግሉ ዘርፍ የሚቀርቡ የግብርና  ኤክስቴንሽን  አገልግሎቶችን  የሚያስከፍሉበት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ይህ የተገለጸዉ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ኤክስቴንሸን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ጋር በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ባደረገው የአስረጂዎች መድረክ ላይ ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ  ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት፤ ረቂቅ አዋጁ ሀገሪቱ  የተያያዘችውን የግብርና ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ሰብል ራሳችንን ለመቻልና የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡

ረቂቁ በሚጸድቅበት ወቅት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ መንግስት ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጨማሪ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን የሚያሳትፍ በመሆኑ ዘርፉ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያየ ብቃትና እውቀት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው አካላት እንዲሳተፉ የሚስችል ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መለሰ መኮነን ፤ አዋጁ ያስፈለገበት ዋና አላማ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር በግብርና ልማትና በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ያለውን የተደራሽነት፣ የጥራት፣ የአቅም እንዲሁም የአፈጻጸም ውስንነት ለመቅረፍ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ነው ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሲጸድቅ በመንግሥት ብቻ ሲሰጥ የቆየውን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ወይም የሙያ ማሕበራት በመመዝገብና በማቀናጀት ደረጃውን የጠበቀ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የግብርና ኤክስቴንሽን  እንዲኖር እንደሚያስችልም  ሚንስትር ደዔታው ተናግረዋል፡፡

ለዓለም አሰፋ

ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *