የዲሞክራሲ ተቋማት የቢሮ ኪራይ ወጪ ከበጀታቸዉ ትልቁን ሽፋን የሚይዝ ነዉ ተባለ

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቢሮ ኪራይ ወጪ እንደተፈተኑ ተነግሯል።

ይህ የተባለዉ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባው በፌዴራል መንግስት የ2018 ረቂቅ በጀት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነዉ።

የምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ  ዘሃራ ቢፍቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ያለባቸዉን የፋይናንስ እጥረት አስመልክተው አራት ተቋማትን በምሳሌነት አንስተዋል።

የምክር ቤት አባሏ በምሳሌነት ያነሱት የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም 80 በመቶ ወጪዉ ለቢሮ ኪራይ የሚዉል መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን 1ሺህ 545 ያህል ባለሙያዎች እያስፈለገዉ  ቅርጫፎች ፅህፈት ቤቶቹን ጨምሮ 300 ባለሙያዎች ብቻ እንዳሉት ገልፀዋል።

ተቋሙ ባለፉት አመታት ዉስጥ ሰራተኞች እንደለቀቁበት የተገለፀ ሲሆን ተመጣጣኝ ክፍያ እየከፈሉ ባለመሆኑ ነባር ሰራተኞችም እየለቀቁ ነዉ ተብሏል።

በምሳሌነት ከተነሱት ዉስጥ የሆነዉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሌላኛዉ ሲሆን የአካባቢዊ ምርጫን ለማካሄድ ተመሳሳይ የበጀት ጥያቄዎችን እንደሚያነሳ የምክር ቤት አባሏ ተናግረዋል።

በግንቦት ወር ማገባደጃ ቦርዱ ለጋዜጠኞች በሰጠዉ መግለጫ በኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የአካባቢ ምርጫ አለማካሄዱን ገልፆ ነበር።

ይህንን ዓመት ጭምር በመስከረም ወር ላይ በአራት ቦታዎች ማለትም በሁለት ከተሞች እና በሁለት ክልሎች ላይ የአካባቢያዊ ምርጫ ለማከናወን በጀት አስጠንቶ የነበረ ቢሆንም ሳይካሄድ መቅረቱን መናገሩ ይታወሳል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸዉ የተቋማት በጀት የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት  እንደነበር  ገልፀዋል።

የዲሞክራሲ ተቋማቱን በጀት በድጋሚ ለማየት እንደሚቻልም ጠቁመዋል ሆኖም  እንደ ሀገር ከሌሎች ተቋማት የተለየ ክፍያ የሚደረግበት ሁኔታ  የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቁምነገር አየለ

ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *