ትራምፕ ቀደም ሲል በዩክሬይን ያለውን ጦርነት በአንድ ቀን ውስጥ መፍትሄ አመጣለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸዉ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ትራምፕ ለሁለተኛ ዘመነ ስልጣን ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት ከተመለሱ በኋላ ዩክሪንን ወራ እያጠቃች ካለችዉ ሩስያ ጋር የሰላም ውይይት ለመጀመርና ፤ የተኩስ አቁም ለማድረግ ያደረጉት በአብዛኛው ጥረታቸዉ አልተሳካም።
ሩስያ ባለፈው ሳምንት ትራምፕና ፑቲን የስልክ ውይይት ካደረጉ ከሰዓታት በኋላ በዩክሬይን ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በሩስያው መሪ በፑቲን ላይ ያላቸውን “ቅሬታ” ገልጸዋል።
በከሩስያ ጋር የሚካሄደዉ የሠላም ድርድር መፍትሄ እያጣ መሄዱን ተከትሎ፣ ትራምፕ ተጨማሪ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን እንደሚልኩ በሳምንቱ መጀመርያ ሰኞ እለት አስታውቀዋል።
ትራምፕ እንደተናገሩት አሁን ሞስኮ በ50 ቀናት ውስጥ የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በሩሲያና በንግድ ሽሪኮችዋ ላይ የታሪፍ ጭማሪና ማዕቀብ እጥላለሁ ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።
ይህ ጥብቅ አቋም ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥን ያመለክታል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ትራምፕ የሩስያን አመለካከት በማንጸባረቅ ጦርነቱን ያስጀመረችዉ ዩክሬን ናት፤ ጥፋተኛዋም ዩክሪን ናት ማለታቸዉ ይታወሳል።
ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
