ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እየተበረዙ በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባልም ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ለባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ቀና አመለካከት ያለው በመሆኑ ከህግ ባሻገር በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት፤ የቀደሞ የታሪክ መምህር፣ የባህል፣ቱሪዝም ጥናትና ምርምር ባለሙያው አማን ኑርዬ ናቸው፡፡
በከምባታ ዞን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ጋሽ አማን፤ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ቅራኔዎችን ከሆድ አጥቦ ለማውጣት የሚያግዙ በመሆናቸው ዛሬ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ የማበጀት አቅማቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የከምባታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል፣ ታሪክ ጥናትና ልማት ዋና የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ደስታ ዘለቀ፤ ግጭቶች በህግ የሚፈቱበት መንገድ ቢኖሩ እንኳ ከፍርድ ቤት በላይ በማህበረሰቡ ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጋሽ አማንም ሆኑ አቶ ደስታ አሁን ላይ የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እየተበረዙ እንደሚገኙ ገልፀው፤ ለዚህ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በአንዳንድ ሽማግሌዎችም ሆነ በተሸማጋዮች ዘንድ ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶች መስተዋላቸው ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አዲስአለም አበበ
ሀምሌ 15/2017 ዓ.ም
