በስዊድን ሰሜናዊ ጫፍ በምትገኘው ኪሩና ከተማ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጋረጠባት የ1መቶ13 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆነች ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ቦታ እየተዛወረች ነው።
ጉዞው 5 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል ተብሏል።
የኪሩና ቤተክርስቲያን 35 ሜትር ከፍታ፣ 40 ሜትር ስፋት እና 6መቶ72 ቶን ክብደት አላት።
ይህች ግዙፍ የቀይ እንጨት ህንጻ በ1912 የተገነባች ሲሆን፤አሁን በግዙፍ ተንቀሳቃሽ መድረኮች ላይ ተጭና ወደ አዲሱ የከተማው ማዕከል ጉዞ ጀምራለች፡፡
በሰዓት ቢበዛ 5መቶ ሜትር እየተጓዘች ሲሆን፤ጉዞው ሁለት ቀናትን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የድሮው የከተማው ማዕከል ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ በቆየ የብረት ማዕድን ቁፋሮ ምክንያት በመሬት መሰንጠቅ አደጋ ስር ወድቋል።
በስዊድን ህግ መሰረት ደግሞ በማንኛውም ህንጻ ስር የማዕድን ቁፋሮ ማካሄድ አይቻልም።
የቤተክርስቲያኗ መዛወር በኪሩና ከተማ ውስጥ እየተከናወነ ካለው ህንጻዎችን የማዛወር ሰፊ ፕሮጀክት እጅግ አስደናቂዉ እና ተምሳሌታዊ ክስተት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የማዛወር ስራውን በበላይነት የሚመሩት የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ፤ብዙ ዝግጅት አድርገናል ይህ ታሪካዊ ክስተት ነው፤በጣም ትልቅ እና ውስብስብ ኦፕሬሽን ሲሆን፤ ለስህተት ቦታ የለንም ነገር ግን ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ነው ብለዋል፡፡
ከማዛወሩ ሂደት እጅግ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የቤተክርስቲያኗን የውስጥ ውድ ቅርሶች መጠበቅ ይገኝበታል።
በተለይም የስዊድን ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በነበሩት በልዑል ዩጂን የተሳለው ታላቁ የመሠዊያ ሥዕል ጥበቃ ይፈልጋል።
የኪሩና የልማት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤በመሬት መሰንጠቅ ሰዎች ሊወድቁ ይችላሉ የሚል ስጋት የለም። ነገር ግን መሰንጠቆቹ በሂደት የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና የፍሳሽ መስመሮችን ያበላሻሉ። ስለዚህ የመሰረተ ልማት አውታሮቹ ከጥቅም ውጪ ከመሆናቸው በፊት ሰዎች መዛወር አለባቸው ብለዋል።
ይህች ቤተክርስቲያን በአንድ ወቅት ከ1950 በፊት ከተሰሩ የስዊድን ህንጻዎች ሁሉ እጅግ ውብ ተብላ ተመርጣ ነበር።
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ትልቁ ፈተና ለእንዲህ አይነቱ ሰፊ ህንጻ መንገዱን ማዘጋጀት ነበር ይላሉ።
መንገዱን ወደ 24 ሜትር አስፍተነዋል፤ በጉዞው መስመር ላይ የነበሩ የመንገድ መብራቶችን፣ የትራፊክ መብራቶችን እንዲሁም አንድ ድልድይ አስወግደናል ብለዋል፡፡
የብረት ማዕድን አውጪው ኩባንያ የከተማዋን የማዛወር ወጪ የሚሸፍን ሲሆን፤ይህም ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚገመት ተነግሯል።
የስዊድን ቴሌቪዥን ይህንን ጉዞ በቀጥታ እያስተላለፈው መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 13 /2017 ዓ.ም
