የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት ለፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ የሩስያን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ለዩክሬን ደህንነት ዋስትና እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህን ቃል የገቡት አርብ ዕለት በአላስካ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ ዜሌንስኪን እና የአውሮፓ አጋሮቻቸውን ቡድን ባስተናገዱበት በዋይት ሐውስ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው።
በዚህ ጉባኤ ላይ ለመካፈል በርካታ የአውሮፓ አገር መሪዎችም የተጓዙ ሲሆን፤ ንግግሩ የትራምፕ እና የፑቲን የአላስካ ጉባዔ ያለ ተኩስ አቁም ስምምነት በተጠናቀቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተካሄደ ነው።
“ዩክሬን በሰላም መንገድ ላይ መቼም አትቆምም” ብለዋል ዘሌንስኪ ፡፡
አውሮፓ የትራምፕን የደህንነት ዋስትና ስትቀበል ዜለንስኪ ለፑቲን ንግግር ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡
ስፍራው ወደፊት ይገለፃል የተባለው የሁለትዮሽ ውይይት ከተደረገ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚሳተፉበት የሦስትዮሽ ንግግር እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የፑቲን አማካሪ ትራምፕ እና ፑቲን ለ40 ደቂቃ በስልክ መነጋገራቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ከደህንነት ጋር በተያያዘ ብዙ እርዳታ ይኖራል” ሲሉ የአውሮፓ አገራት ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።
“እነሱ እዚያ ስላሉ የመጀመርያው የመከላከያ መስመር ላይ ናቸው። ነገርግን እንረዳቸዋለን።
በዚህ ንግግራቸው ስለ እርዳታው ዓይነት እና መጠን ይፋ ያደረጉት ነገር የለም።
ዜሌንስኪ የተገባውን ቃል “ትልቅ እርምጃ” በማለት አሞካሽተው ዋስትናዎቹ “እስከ 10 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ በወረቀት ላይ ይሰፍራሉ” ብለዋል።
አክለውም ዩክሬን ወደ 90 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአሜሪካን ጦር መሣርያ ለመግዛት እንደምትፈልግ ተናግረዋል
ሞስኮ የፑቲን እና ዜሌንስኪን ንግግር በተደጋጋሚ እንደማትቀበል ስትገልፅ ቆይታለች።
ነሐሴ 13 /2017 ዓ.ም
