በአርሶ አደሩ ዘንድ ስለግብርና ውል ምርት (Contract Farming) ያለው ግንዛቤ በቂ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኩባንያዎችን ፍላጎት ካላቸው አርሶ አደሮችና ማኅበራት ጋር የማስተሳሰር ዓላማ አድርጓል የተባለው የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣው አዋጅ በሰኔ 2015 መጨረሻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስቴርም አዋጁን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የአሰራር መመሪያ በማዘጋጀት በሁሉም ክልሎች መዋቅር እየዘረጋሁ ነው ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ግን አርሶ አደሩ በግብርና የውል ምርት ለመስራት ፈቃደኝነቱ እምብዛም መሆኑን ነግረውናል፡፡
የላንድ ማርክ አግሮ ፋርሚንግ ባለቤት መክብብ ቶልቺሳ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ አርሶ አደሩ የሚዘራው ምርት የምግብ ፍጆታ ላይ ያተኮረ ካልሆነ በሌሎች ምርቶች ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ነግረውናል፡፡
ድርጅታቸው ለህክምና አገልግሎት የሚውሉና ጥሩ መዓዛ ያላቸው (አሮማቲክ) ተክሎች ላይ እንደተሰማራ ገልፀው አርሶ አደሩ አብሮን እንዲሰራ የማሳመን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ መክብብ ገፃ ተክሎቹ የአርሶ አደሩን ህይወት መለወጥ የሚችሉ ምርቶች ናቸው፡፡ ስራችንን ለማስፋትና የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ግን የመሬት ችግር እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመሬት ጥያቄያችን ምላሽ ቢያገኝ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንችላለን ሲሉም አክለዋል፡፡
አዲስአለም አበበ
ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም
