ዋሽንግተን በብዙ የህንድ ምርቶች ላይ ታሪፍ በእጥፍ ለመጨመር መወሰኗ ለህንድ ትልቁ የዉጭ ገበያ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ህንድ በቅናሽ ዋጋ የሩሲያ ነዳጅ በመግዛቷ ከህንድ በሚገቡ ብዙ ምርቶች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ ወደ 50 በመቶ ከፍ አድርገናል ብለዋል።
ዛሬ ስራ ላይ የዋለው ይህ ከፍተኛ ታሪፍ፤ ህንድ ከትልቁ የኤክስፖርት ገበያዋ አሜሪካ ጋር የምታደርገዉን ንግድ አደጋ ላይ በመጣል በህንድ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል።
ህንድ በ2024 ከ87 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ልካለች።
ይህን እርምጃ ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ያልተገባ እና ምክንያታዊ ያልሆነ በማለት የነቀፈው የህንድ መንግስት፤ ታሪፉ ከ48 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን እንደሚጎዳ ገልጿል፡፡
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ በወዳጅ እና ተወዳዳሪ ሲሉ በጠሯቸዉ አገራት ላይ በተጣሉ ተጨማሪ ቀረጦች፤ አሜሪካ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በህንድ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥላ ነበር።
ኒውዴልሂ የሩሲያን ነዳጅ በመግዛቷ ለመቅጣት የተወሰደ እርምጃ ነዉ ያሉት ትራምፕ፤ ይህ በተዘዋዋሪ የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት መደገፍ ነዉ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ህንድ ከውጭ ካስገባችዉ ድፍድፍ ነዳጅ ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆነው ከሩሲያ የመጣ ሲሆን፤ ይህ የንግድ ግንኙነት ከዋሽንግተን ትችት አስነስቷል።
ይህ እርምጃ የህንድ ላኪዎች ካጋጠማቸዉ በውጭ ሀገራት ምርቶች ላይ ከተጣሉ ከፍተኛ ታሪፎች አንዱ ሲሆን፤ብራዚልም በብዙ የኤክስፖርት ምርቶቿ ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ እንደተጣለባት የሚታወስ ነዉ ሲል አልጀዚራ ነዉ የዘገበዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 21 /2017 ዓ.ም
