የአዲሱ የውድድር ዘመን የቱርክ ሱፐር ሊግ ከተጀመረ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ነው ፖርቹጋላዊው የስንብት ደብዳቤው ዛሬ የደረሳቸው፡፡
በተለይም ደግሞ ከትናንት ወዲያ (ረቡዕ) በምንግዜም ተቀናቃኛቸው ቤኒፊካ የደረሰባቸው የ1-0 ሽንፈትና በቻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት አለመቻላቸው ለስንብታቸው ዋና ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
ፌኔርባቼ ዛሬ ረፋድ በኤክስ ገፁ ባወጣው መግለጫ “ክለባችን ከ2024/25 የውድድር ዘመን ጅማሬ አንስቶ ዋና አሰልጣኛችን ከነበሩት ጆዜ ሞውሪንሆ ጋር ተለያይቷል፡፡
ከእኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እያመሰገንን መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው እንመኝላቸዋለን” ብሏል፡፡
የ62 ዓመቱ ሞውሪንሆ ፌኔርባቼን የተረከቡት በግንቦት 2024 ነበር፡፡ የሁለት ዓመት ኮንትራት የነበራቸው ቢሆንም ከትናንትና ወዲያ በስታዲዮ ዳ ሉዝ በቤኒፊካ የደረሰባቸው የ1-0 ሽንፈት ግን ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ያላቸው እህል ውሃ እንዲያበቃ አድርጓቸዋል፡፡
“Spor Arena” የተባለው የቱርክ ሚዲያ እንደዘገበው ከሆነ ሞውሪንሆ የክለቡ ቦርድ በክረምቱ የዝውውር መስኮት እየተከተለ ባለው አካሄድ ደስተኛ አይደሉም፡፡ የክለቡን ስትራቴጂም ሲተቹ ቆይተዋል፡፡
በተለይም ደግሞ በቅርቡ “ፌኔርባቼ የሚያዘዋውራቸውን የተጨዋቾች ዝርዝር የያዘበት መዝገብ የጠፋበት ይመስለኛል” ሲሉ የሰጡት አስተያየት በክለቡ ሃላፊዎች ጥርስ ሳያስነክስባቸው እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
ስንብታቸውን ተከትሎ የቀድሞ ክለባቸው ማን.ዩናይትድ ሩበን አሞሪምን የሚያሰናበት ከሆነ ሞውሪንሆን መልሶ ሊቀጥራቸው ይችል ይሆናል የሚሉ ወሬዎች መሰማት ጀምረዋል፡፡
ምስጋናው ታደሰ
ነሃሴ 23/2017 ዓ.ም
