የሐማስ ቃል አቀባይ አቡ ኦቤይዳ በጋዛ በአየር ጥቃት መገደሉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ለዚህ ግድያ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን እንዲሁም የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ፣ ሺን ቤትን አመስግነዋል።

ሚኒስትሩ “እንከን የለሽ አፈጻጸም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።ሐማስ የቃል አቀባዩን ግድያ እስካሁን አላረጋገጠም።

እሰራኤል በጋዛ ሰርጥ በመኖሪያ ህንጻ ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ቀደም ሲል ሐማስ አስታውቆ ነበር።

በጋዛ ከተማ ህዝብ በሚጨናነቅባት አል ሪማል ሰፈር ላይ የእሰራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 20 መቁሰላቸውን የአካባቢው ጋዜጠኞች ዘግበዋል።
በዚህ ጥቃት ከተገደሉትም ህጻናት ይገኙበታል።

የቅዳሜው ጥቃት የተፈጸመው እስራኤል በጋዛ ከተማ ሙሉ ወረራ የመፈጸም እቅዷን ተግባራዊ ከማድረጓ በፊት ነው።

ካትዝ በርካታ ተጨማሪ የኦቤይዳ “ወንጀለኛ አጋሮች” በቀጣዩ “ተጠናክሮ በሚቀጥለው የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ” ኢላማ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

ካትዝ የገለጹት “ዘመቻ” እስራኤል የጋዛ ከተማን በሙሉ ለመውረር በቅርቡ በካቢኔዋ የጸደቀውን ዕቅድ ነው ።

የእስራኤል መከላከያ እና ሺን ቤት የሐማስ ቃል አቀባይን ስለገደለው ጥቃት ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን ባወጡት መግለጫ ሰጥተዋል።
ግድያው ሊሳካ የቻለው ቃል አቀባዩ የተደበቀበትን ቦታ ለመለየት በሺን ቤት እና በመከላከያ ሰራዊቱ በተሰበሰበ መረጃ እንደሆነ በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

ኦቤይዳ በህይወት ከቀሩት የሐማሰ ወታደራዊ ክንፍ ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ነበር።
በአል ሪማል ሰፈር ህንጻ የሚገኘውን ባለ ስድስት ፎቅ አፓርታማ አምስት ሚሳኤሎች ከሁለት አቅጣጫ መምታታቸው ተነግሯል።

የህንጻው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ፎቅ ኢላማ መደረጉ ተገልጿል።ህንጻው የጥርስ ቀዶ ሃኪም አገልግሎት መስጫነት ያገለግላል ተብሏል።

የተቋማቱ የጋራ መግለጫ ኦቤይዳ “የሐማስ አሸባሪ ድርጅት የህዝብ ፊት ሆኖ አገልግሏል” እንዲሁም “የሐማስን ፕሮፖጋንዳ ያሰራጭ ነበር” ብሏል።

ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *