የመስቀል በዓልን ለማክበር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው የሚጓዙ እንግዶች ያለምንም እንግልትና የትራፊክ አደጋ ገብተው እንዲያከብሩ በቅንጅት እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታዉቋል ፡፡
የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ለተጓዦች የእንኳን ደህና መጣችሁ ያሉ ሲሆን ባለፉት ሶስትና ሁለት አመታት ማህበረሰቡ በዓላቶቹን ለማክበር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው በሚገቡበት ወቅት ከፍተኛ እንግልት እንደነበር አስታውሰዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ የዞኑ መንግስት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አመራሮችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ የትራፊክ ፍሰቱ ፍጹም ሰላማዊና ጤናማ በመሆኑ ተጓዦች ደስተኛ ሆነው ወደ ቀዬአቸው እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ግሩም ወልደሰንበት በበኩላቸዉ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የጸጥታ አካላትና የዘርፉ አመራሮች ተጓዦች ሳይንገላቱ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው እንዲገቡ እየሰሩት ያለው ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ መናገራቸዉን የዞኑ መንግስት ኮምኒኬሽን አስታዉቋል ፡፡
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ እስከ ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ማንም ሳያስቆማቸውና በሰላማዊ መልኩ እየገቡ መሆኑን አንስተው ይህም ውጤት እንዲመጣ ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።
አቤል እስጢፋኖስ
መስከረም 14/2018 ዓ.ም
