ወጋገን ባንክ አ.ማ. መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት ያካሄደ ሲሆን፤ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን ባንኩ በ2024/25 በጀት ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 13.5 ቢሊየን ብር ገቢ እንዳስመዘገበ አስታውቀዋል።
ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38 በመቶ እድገት እንደሚያሳይ እና የአንድ አክሲዮን ትርፍ ወደ 46.10 በመቶ ማደጉን የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
በተጠቀሰው በጀት ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት የ 3.85 ቢሊየን ብር ትርፍ እንዳገኘ እና ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ73 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም የባንኩ ባለአክሲዮኖች ብዛት ወደ 14ሺህ 8መቶ71 ማደጉን እና የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ብልጫ በማሳየት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 84.7 ቢሊየን ብር ማደጉን አንስተዋል፡፡
ባንኩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የዲጂታል ብድር አገልግሎቶችን በበጀት ዓመቱ ያቀረበ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና በሴቶች አካታችነት ዙሪያ ባደረገው ምዘና ውጤት መሰረት ወጋገን ባንክ ከ30 የግል ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ደረጃ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በመላው ሀገሪቱ የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን ለመደገፍ እና በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ለሚስሩ በጎ አድራጎት ተቋማት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ አብዲሹ ገልፀዋል።
ሀመረ ፍሬው
መስከረም 27/2018 ዓ.ም
