የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ ኦሮሚያ ባንክ እና ኳንተም ቴክኖሎጂ አ.ማ፤ ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎትን በመጠቀም በአሁን ይብረሩ፤ በኋላ ይክፈሉ (Fly Now, Pay Later) መርኃ-ግብር አብሮ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነትን ተፈራርመዋል፡፡
ኦሮሚያ ባንክ ሀገራችን የያዘችዉን የዲጂታል ኢትዮጵያ መሪ እቅድ ለመደገፍ እና የዲጂታል ግብይቱን ተደራሽነት ለማስፋት ፣ ከኳንተም ቴክኖሎጂ ጋር በትብብር የበለጸገውን ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያን በመጠቀም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ኦሮሚያ ባንክ ከሁለቱ ተቋማት ጋር በጋራ ከተስማማባቸዉ ጉዳዮች አንዱ፤ ባንኩ በቅርቡ ስራ ላይ ያዋለዉን ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ በመጠቀም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች ገንዘብ ቢያጥራቸዉ ያለምንም ማስያዣያ እና ዋስትና በሚልኪ ተበድረዉ የበረራ ቲኬት በመቁረጥ ከበረሩ እና ጉዳያቸዉን ከፈፀሙ በኋላ ተረጋግተዉ የሚከፍሉበት አይነተኛ አማራጭ ማመቻቸት ላይ ነው፡፡
አሁን ይብረሩ፤ በኋላ ይክፈሉ የተሰኘው መርኃ-ግብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች ጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት ሳያሳስባቸዉ ሚልኪ መተግበሪያን በመጠቀም የአየር ቲኬታቸዉን በመቁረጥ ሀገር አቀፍም ሆነ አለም አቀፍ በረራዎችን ካከናወኑ እና ጉዳያቸዉን ከፈፀሙ በኋላ ስራቸዉን እየሰሩ እንዲከፍሉ እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡
የሶስቱ ተቋማት እስትራቴጂካዊ አጋርነት የጥሬ ገንዝብ ዝዉዉርን በመቀነስ የሀገራችንን ዲጂታላይዜሽን ጉዞ ከማዘመን እና የፋይናንስ አካታችነትን ከመደገፍ በተጨማሪ የዜጎችን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በእጅጉ ያሳልጣል ተብሎ እንደሚታመን ተገልጿል፡፡
አቤል እስጢፋኖስ
መስከረም 28/2018 ዓ.ም
