ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ሐዋርያዊ ተግባራትን ለመምራትም ሆነ ለማከናወን የማያስችል ምንም ዓይነት የጤና እክል እንዳልገጠማቸው እና ከዚሁ ጋር በተያያዘም ያቀረቡት ጥያቄ የሌለ መሆኑን ፅ/ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ እንዳመላከተው ከሰሞኑን ድብቅ አጀንዳ ይዘው ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት መደበኛውን የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ማደናቀፍ ዓላማቸው ያደረጉ አካላት በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው ፍጹም ከእውነት የራቀ መረጃን አሰራጭተዋል ብሏል።
ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ተግባራትን ለመምራትም ሆነ ለማከናወን የማያስችል ምንም ዓይነት የጤና እክል አልገጠማቸውም ያለው መግለጫው ከዚሁ ጋር በተያያዘም ያቀረቡት ጥያቄ የሌለ መሆኑን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ወደ ሰሜን አሜሪካ በማምራት የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸው ያስታወቀ ሲሆን በቅርቡም ተመሳሳይ ጉዞ አድርገው ጳጉሜን 1 ቀን 2017 ዓመተ ምሕረት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በታላቅ ክብር መመለሳቸው እና ለአዲስ አመት ዘመን መለወጫ እንዲሁም ለመስቀል በዓል አባታዊ ቃለ በረከትና ቡራኬ ማስተላለፋቸውን አስታውሷል።
ዘገባው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ነው
መስከረም 29/2018 ዓ.ም
