በትግራይ ክልል ከጦርነት በኋላ በተፈጠረ የሥነ አዕምሮ ቀውስ በርካቶች መቸገራቸው ተነግሯል።
በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር አበራ ተፈራ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአዕምሮ ቀውስ ላጋጠማቸው የጦርነቱ ሰለባዎች ሁሉም ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በተለይ የጤና ሚኒስቴር በድህረ ጦርነት በአዕምሮ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ፕሮጀክት ነድፎ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ለከፍተኛ የሥነ አዕምሮ ቀውስ የተዳረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉበትን ሁኔታ የሚያመላክት ጥናት ይፋ ተደርጓል።
ጥቅምት 4፣ 2018 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ጥናቱ፤ በአውሮፓ ህብረት ትረስት ፈንድ እና CST ኢትዮጵያ ትብብር እንደተከናወነ የሳይኮሎጂ መምህሩ ነግረውናል።
በመቀሌ እና በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በተከናወነው ጥናት በተለይም እንደ ኢሮብ፣ ዛላንበሳ፣ አዲግራት እና ጉሎ መኸዳ በመሳሰሉ አካባቢዎች ዜጎች ለከፍተኛ የሥነ አዕምሮ ቀውስ መዳረጋቸው ተገልጿል።
አካባቢዎቹ ከአስርት ዓመታት በፊት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች ጦርነት ገፈቱን የቀመሱ በመሆናቸው ነዋሪዎቹ ለተደጋጋሚ የስነ-አዕምሮ ቀውስ መጋለጣቸው ተነግሯል።
ስለሆነም በተደጋጋሚ ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተረባርበው ከገቡበት ቀውስ እንዲወጡ መስራት እንደሚገባ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህሩ አበራ ተፈራ አሳስበዋል። በተለይ የጤና ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
አዲስአለም አበበ
ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም
