በመዲናዋ ፆታዊ ጥቃት ከሚደርስባቸው መካከል 90 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል
ከእነዚህ መካከል ደግሞ 70 በመቶዎቹ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ናቸው ተብሏል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄለን አዱኛ ፤ በመዲናዋ ጥቃት የሚደርስባቸው ልጆች ቁጥር ከፍ ማለቱን ነግረውናል።
ጥቃቱ በአብዛኛው በቅርብ ቤተሰብ፣ ዘመድ ይደርሳል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ 40 በመቶ አከባቢ የሚሆነው በመንገደኛ ወይም ባልታወቁ ሰዎች የሚፈፀም ነው ብለዋል።
ጥቃት ከሚደርስባቸው መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች መሆናቸውን ያነሱት ወ/ሮ ሄለን፤ ጥቃትን ለአንድ አካል ብቻ የምንሰጠው አይደለም ብለዋል።
ጥቃት ደርሶባቸዋል ወደ ህክምና ተቋማት ከሚመጡት መካከል ቁጥሩ ከፍተኛም ባይሆን የኤችአይቪ እና የአባላዘር ህመሞች እንደሚገኙባቸውም አንስተዋል።
ጥቃት ደርሶባቸው ለሚመጡ በአዲስ አበባ አራት ተቋማት ላይ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀው፤ ተቋማቱም ምንሊክ ፣ አበበች ጎበና፣ ጋንዲ እና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም
