በኢትዮጵያ ያሉ የፅሁፍ ቅርሶች ስንት እና የት ናቸዉ የሚለዉን ለማወቅ የተሰነደ መረጃ እምብዛም ነዉ ተብሏል።
ከሀያ አመት በፊት የተመዘገቡ አስራ ሁለት ብቻ የፅሁፍ ቅርሶች በአለም የትዉስታ ማህደር ተመዝግበው የሚገኙ ናቸዉ ተብሏል።
የዚህ የፅሁፍ ቅርስ ምዝገባ ሂደት ከተቋረጠም ሀያ አመታት ማስቆጠሩ ተነግሯል።
ሀገሪቱ ያላትን የፅሁፍ ቅርሶች የመጠበቅ እና የማስመዝገብ ስራን ለማስተባበር ይሰራል የተባለ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ተነግሯል።
በዛሬዉ ዕለት ይህ የብሄራዊ የፅሁፍ ቅርስ አስመዝጋቢ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ የማድረጊያ ስነስርአት በኢትዮጵያ ቤተመጻሕፍት እና ቤተመዛግብት አገልግሎት ተካሂዷል።
ሀገሪቱ በአለም ቅርስነት ሊመዘገቡ የሚችሉ የፅሁፍ ቅርሶች ቢኖሯትም ከፈረንጆቹ 1997 ወዲህ አዳዲስ የፅሁፍ ቅርሶችን አላስመዝገበችም ተብሏል።
ዛሬ መቋቋሙ ይፋ የተደረገዉ የብሔራዊ የፅሁፍ ቅርስ አስመዝጋቢ ኮሚቴ፤ ከ2026 እስከ 2027 በአለም የትዉስታ ማህደር እንዲመዘገቡ በእጩነት ሊቀርቡ የሚችሉ የፅሁፍ ቅርሶችን መለየቱ ተገልጿል።
ለእነዚህ የፅሁፍ ቅርሶችም ለመመዝገብ የሚያስችላቸዉን ደጋፊ ሰነዶች በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።
የኮሚቴዉ አባል ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት፤ እስካሁን ከተመዘገቡት አስራ ሁለቱ ዉጭ በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ማስመዝገብ የሚቻልበት ዕድል እንደነበር ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ተመዝግበዋል የተባሉ የፅሁፍ ቅርሶች የነገሥታት ደብዳቤዎች እና ጦማሮች ሲሆኑ፤ ዘመናቸዉ ከ19ኛዉ እና 20ኛዉ ክፍለዘመን የተሻገሩ አይደሉም ተብሏል።
የፅሁፍ ቅርሶቹን ለመጠበቅ ÷ ለመንከባከብ እና የማስተዋወቅ እና በአለም የትዉስታ ማህደር የማስመዝገብ ስራን ይሄ ይፋ የተደረገው ብሄራዊ ኮሚቴ የሚያስተባብረዉ ይሆናል ተብሏል።
ቁምነገር አየለ
ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም
