“የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ አገልግሎት” የተሰኘው ፕሮጀክት በምስራቅ አፍሪካ ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አስመዝግቦ መጠናቀቁ ተገለጸ
በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ለመደገፍ “የመሬት፣ የአፈር እና የሰብል መረጃ አገልግሎቶች” የተሰኘው ይህ ፕሮጀከት ለአራት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሩዋንዳ ያስገኘውን ውጤቶችና የተገኙ ልምዶችን ይፋ አድርጓል።
በአውሮፓ ህብረት በዴቨሎፕመንት ስማርት ኢኖቬሽን ስር የሚገኘው የግብርና ምርምር ፕሮግራም(DeSIRA) ፣ በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በISRIC በጋራ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ይህ ፕሮጀከት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ፤ በኬንያና በሩዋንዳ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
የዚህ ፕሮግራም ዓላማ በሀገራዊ የምርምር ተቋማት ውስጥ ዘላቂነት ያላቸውን የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ ማዕከላትን በማቋቋም ሀገራዊ የግብርና እውቀትና ፈጠራ ሥርዓቶችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል ፡፡
እነዚህ የመረጃ ማዕከላት ባለፉት አራት ዓመታት የተሰበሰበው መረጃ በማቀናበርና በማስተሳሰር፤ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥን የሚያጎለብቱ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን መረጃው ለባለድርሻ አካላት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚያስችል ተነግሯል ፡፡
“የፈጠርናቸው አጋርነቶች፣ ያስተዋወቅናቸው ፈጠራዎች እና ያካፈልነው ዕውቀት ሊቀጥሉ የሚገባቸው መልካም ሁኔታዎች ናቸው፤ ለሁሉም የገንዘብ ደጋፊዎች እና ለሀገር ውስጥ አጋሮቻችን ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር አበራ ደሬሳ ተናግረዋል
የፕሮጀክቱ ቁልፍ ውጤቶች ይፋ የሆኑ ሲሆን ማዕከል ማቋቋም ፤አቅም ግንባታ እና በተጠቃሚዎች ላይ የተገኙ ለውጦች በጉልህ የተነሱ ሆነዋል
አቤል እስጢፋኖስ
ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም
