ኢ-ፋይቶ የተሰኘው አገልግሎቱ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሂደትን ፈጣንና ደህንነቱ የተጠበቀ ያደርገዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ማረጋገጥ ያስችላሉ ያላቸውን ሁለት ፕሮግራሞች ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ጋር በጋራ ይፋ አድርገዋል።
የእጽዋት ጤና የምስክር ወረቀት በኤሌክትሮኒክ የሚሰጥበት “ኢ-ፋይቶ” ከተሰኘው ስርዓት በተጨማሪ “ማኅበር” የተሰኘ የኢትዮጵያን ሆርቲካልቸር ዘርፍ ተወዳዳሪነት፣ የጥራት ደረጃንና ዘላቂነትን ለማሳደግ ያለመ ፕሮግራምም ይፋ ተደርጓል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መለሰ መኮንን በዚሁ ወቅት፣ የእንሰሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት ለውጭ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
የእንሰሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ (SPS) የዓለም አቀፍ ንግድ ደህንነትንና ጥራትን የሚያረጋግጥ ስርዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዓለም አቀፍ ንግድና ለባዮሴኩሪቲ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮግራሞቹ መጀመር የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ተጠቅሷል። የኢ-ፋይቶ ስርዓት በወረቀት ላይ የተመሠረተውን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመተካት ለኤክስፖርት ንግድ ቅልጥፍና፣ ግልጽነት እና አስተማማኝነት በእጅጉ ያግዛል ተብሏል፡፡
ፕሮግራሞቹ በተለይም የሆርቲካልቸር ዘርፉን ለማጠናከር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአርሶ አደሮችና አምራቾች የተሻለ የገበያ ተደራሽነትን መፍጠር የሚያስችሉ እንደሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
አዲስአለም አበበ
ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም
