“በትክክለኛው መንገድ ከተሰራበት ክብር የሚሰጠው ሙያ ነው” ሲል አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ተናግሯል።
በማሕበራዊ ሚዲያዎች የምንሰራቸው ስራዎች እንደሙያ እየታዩ አይደለም ሲሉ “የኢትዮጵያ ወጣቶች የማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ማህበር” መስራቾች ተናግረዋል።
የማሕበሩ ምስረታ ጥቅምት 27፣ 2018 በሸራተን አዲስ ሆቴል ይፋ በተደረገበት ወቅት መስራቾቹ ባደረጉት ንግግር፣ ለሶሻል ሚዲያ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
ማህበሩ ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዕውቅና ተሰጥቶት እንደተመሰረተም አስታውቀዋል።
ስራው ለእኛ ሙያችን ነው ያሉት መስራቾቹ፣ ማሕበሩ የባለሙያዎቹን ጥቅምና መብት ማስጠበቅ፣ ከጉዳትና ከአላስፈላጊ ተጽዕኖ መከላከል ከተመሰረተበት ዓላማዎች መካከል እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች የማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ማህበር አባላቱ ለቀረጻ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ክልከላና እገዳ እንዳይደረግባቸው መታወቂያ የመስጠት፣ የአባላቱን ገቢ ለማሳደግ የገበያ ትስስር መፍጠር የመሳስሉትም የማሕበሩ ዓላማዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ለማሕበሩ መመስረት አስተዋጽዖ ላደረገው ለማሕበሩ የክብር አባል አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬም ምስጋና አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኘው የማሕበሩ የክብር አባል አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በበኩሉ፣ በአሁኑ ወቅት የሶሻል ሚዲያ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሶ በትክክለኛው መንገድ ከተሰራበት ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ሙያ ነው ብሏል።
አንጋፋ አርቲስቶች በሶሻል ሚዲያው ላይ ተገቢውን እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ሙያው የበለጠ እንደሚከበር ገልፆ እነርሱም መቀላቀል አለባቸው በማለት ተናግሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሌላኛው የማሕበሩ የክብር አባል አርቲስት ጥላጉን ጉግሳም ታድሟል።
አዲስአለም አበበ
ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም
