‹ኪዩር ብላይንድነስ› የተሰኘ ድርጅት 3 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአይን ማከሚያ መሳሪያዎች በዕርዳታ አስረከበ

የኢትዮጵያን የአይን ጤና ህክምና መሠረተ ልማት ለማጠናከር እና  መሰረታዊ የአይን ህክምና መሳሪያዎችን አቅርቦት ለሟሟላት የሚያግዝ ወደ  ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአይን ማከሚያ መሳሪያዎችን ‹ኪዩር ብላይንድነስ› የተሰኘው ድርጅት ለግሷል፡፡

በርክክብ መድረኩ የተገኙት በኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ዘላለም ሀብታሙ፥ሆስፒታሎች በዘመናዊ ላብራቶሪዎች የተግባር ስልጠና በመዉሰድ  የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ ይረዳል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዘላለም፤በኢትዮጵያ በከተማና በገጠር የሚገኙ  የአይን ህክምና መስጫ ማዕከላት የታካሚዎቻቸውን ፍላጎት ባሉበት ሆነዉ እንዲከታተሉ እና ህክምና እንዲሰጡ ይረዳቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የህክምና መስጫ መሳሪያዉ በ36 ዋና ዋና የከፍተኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና የመጀመሪያ ደረጃ የአይን ህክምና መስጫ ተቋማት እንደሚሰራጭም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኬ-ቲ ኦቨርበይ በበኩላቸዉ፤ የኢትዮጵያውያንን የዕለት ተዕለት ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከሶስተኛ ደረጃ ጀምሮ ፣የሁለተኛ  እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ተቋማት ጋር ያለንን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ጥራት ያላቸዉን መሳሪያዎችን ከማቅረብ  በተጨማሪ፤በዘርፉ ላይ ያለዉን ክፍተት ለመሸፈን ከፍተኛ ልምድ ባላቸዉ ባለሙያዎች  የታገዘ ስልጠና በከተማና በገጠር ላሉ የህክምና ተቋማት ሰራተኞች እናዘጋጃለን ብለዋል፡፡

ሀና ሰይፉ

ህዳር 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *