የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሟቹ የወሲብ ንግድ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ፋይሎች በሙሉ እንዲለቀቁ የሚያዘውን ረቂቅ ህግ መፈረማቸውን አስታዉቀዋል።
ህጉ የፍትህ መምሪያው ከኤፕስቲን ምርመራ ጋር የተያያዙ ሁሉንም መረጃዎች በ30 ቀናት ውስጥ ‹‹በሚፈለግ እና በቀላሉ ማውረድ በሚቻል መልኩ›› እንዲቀመጥ ያስገድዳል።
ትራምፕ ቀደም ሲል ፋይሎቹ እንዳይለቀቁ ተቃውመው የነበረ ቢሆንም፤ ከኤፕስቲን ሰለባዎች እና ከራሳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ግፊት ከገጠማቸው በኋላ ባለፈው ሳምንት አቋማቸውን ቀይረዋል።
በእርሳቸው ድጋፍ፣ ህጉ ማክሰኞ ዕለት በሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች (በተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔት) በከፍተኛ ድምፅ ፀድቋል።
ፕሬዝዳንቱ ረቡዕ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ ዴሞክራቶች ይህንን ጉዳይ የያዙት የህዝብን ትኩረት አስተዳደራቸዉ ካመጣዉ ስኬቶች ለማስቀየር ነው ሲሉ ከሰዋል።
እርሳቸውም፤የኤፕስቲን ፋይሎች እንዲለቀቁ የሚያዝዘውን ህግ አሁን ስለፈረምኩ፣ ምናልባት ስለነዚህ ዴሞክራቶች እውነት እና ከጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር ያላቸው ግንኙነት በቅርቡ ይገለጥ ይሆናል ሲሉ ጽፈዋል።
በተወካዮች ምክር ቤት ያሉ ህግ አውጪዎች ህጉን በ4መቶ27 ድጋፍ እና በ1 ተቃውሞ ድምፅ አሳልፈውታል። ሴኔቱም ህጉ እንደደረሰው በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።
ትራምፕን በቀጥታ የሚጠቅሱ አንዳንድ ሰነዶችን ጨምሮ ከኤፕስቲን ንብረት ጋር የተያያዙ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የሰነድ ገጾች ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ይፋ ተደርገዉ ነበር ሲል ቢቢሲ አስታዉሷል።
እስከዳር ግርማ
ህዳር 11/2018 ዓ.ም
