የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና እንዲጎለብት ባለሙያዎች አቅማቸዉን እንዲያሳዩ ተጠየቀ

የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና እንዲጎለብት በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች አቅማቸዉን አዉጥተዉ ማሳየት እንደሚገባቸው የአፍሪካ ጠበቆች ማህበር እና    የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዚዳንት ቴድሮስ ጌታቸዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

አቶ ቴድሮስ በህግ ዘርፉ ተገቢዉ ዝግጅትና ጠንካራ ባለሙያዎችን ማፍራት ካልተቻለ ህግ አቅሙን እንደሚያጣና የተለያዩ ዓላማ ባላቸዉ ግለሰቦች የበላይነቱ እንደሚወሰድበት ገልጸዋል፡፡

ይህም ከሌሎች ሃገራት አንጻር ወደ ኋላ የቀረዉን ዘርፍ ይባስ ይጎዳዋል ሲሉ ነግረዉናል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ የህግ ስምምነቶችን ተቀብላ ፈርማለች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህን የህግ ማዕቀፎች ወደ መሬት አዉርዶ ካለዉ የሃገሪቱ ሁኔታ ጋር አስማምቶ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል፡፡

በተለይም በሃገሪቱ ዉስጥ ያሉ የህግ ባለሙያዎች በአለም አቀፍ የፍትህ ስርዓት ማስከበር ሂደቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ጉባኤዎች ዉስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡

ለዚህ ደግሞ አለም አቀፋዊ ሆነዉ በቀጠናዉ ላይ ተወዳዳሪ እና ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከተቋቋመ ወደ አራት ዓመታት የተጠጋው የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ጠንካራ ባለሙያዎች ያሉት ቢሆንም አቅማቸዉን አዉጥተዉ እየተጠቀሙበት አደለም ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ለጣቢያችን አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ከተቋቋመ ገና አራት ዓመታት ገደማ ቢሆንም ማህበሩ  ያሉትን ክፍተቶች ለመሸፈን፣ ባለሙያዎችን በማብቃትና በህግ አወጣጥ፣ አተረጓጎም እና አተገባበር ዙሩያ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ልዑል ወልዴ

ህዳር 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *