የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 40.8 ሚሊየን ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸዉ ዉስጥ ይገኛል ያለ ሲሆን፤ 64 በመቶው በአፍሪካ ይገኛሉ ብሏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣዉ ይህ አዲስ መረጃ በ2024 መጨረሻ ላይ የተገኘ ነዉ፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ቅነሳ አገልግሎቶችን እያስተጓጎለ እና ኤድስን እንደ ማህበረሰብ ጤና ስጋት ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ጉዞ አደጋ ላይ እንደጣለው ድርጅቱ አስታዉቋል፡፡
ይህ መረጃ ይፋ የሆነው ታኅሣሥ 1 ቀን 2025 የሚከበረውን የዓለም ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በ2024 በአፍሪካ 26.3 ሚሊየን ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸዉ ዉስጥ የነበረባቸዉ ሲሆን፤ በዚሁ ዓመት 6መቶ50 ሺህ አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ተይዘዋል፡፡
3መቶ80 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህይወታቸው አልፏል።
በዚያዉ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.3 ሚሊዮን አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ሲያዙ፣ 6መቶ30 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሞተዋል ነዉ የተባለዉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከ2010 ጀምሮ አዲስ የቫይረሱ ስርጭት በ40በመቶ ፣ እንዲሁም ከኤችአይቪ ጋር የተያያዙ ሞቶች በ54 በመቶ መቀነሳቸውን ጠቅሶ፣ በቅርቡ የተደረጉ የውጭ እርዳታ ቅነሳዎች ግን እነዚህን ድሎች ሊቀለብሱ እንደሚችሉ ያለዉን ስጋት ገልጿል፡፡
ድርጅቱ እየቀነሰ የመጣው የገንዘብ ድጋፍ አገልግሎቶችን እያስተጓጎለ እና በማህበረሰብ የሚመሩ ፕሮግራሞችን ወደ ጎን እየገፋ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
እንዲሁም መገለል፣ መድልዎ እና አግላይ ህጎች የመከላከል እና የህክምና ተደራሽነትን መገደባቸውን ቀጥለዋል ነዉ ያለዉ።
አስቸኳይ እና ቀጣይነት ያለው እርምጃ ካልተወሰደ እ.ኤ.አ. በ2030 ኤድስን እንደ ማህበረሰብ ጤና ስጋት የማጥፋት ግብ እንደማይሳካ ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ህዳር 22/2018 ዓ.ም
