የጊኒ ቢሳው የቅርብ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት አሁንም እልባት አላገኘም።
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እንደገለጸው፤ ታጣቂዎች ቢሮውን ሰብረው በመግባት የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን እና የውጤት መዝገቦችን በመስረቃቸው ህዳር 23 የተካሄደውን አወዛጋቢ ምርጫ ውጤት ማጠናቀቅ አልተቻለም።
ሰርጎ ገቦቹ ውጤቶቹ የተከማቹባቸውን ሰርቨሮችም አውድመዋል ነዉ የተባለዉ፡፡
ተቋሙ እንደገለጸው ዘረፋው የተፈጸመው ይፋዊ የምርጫ ውጤቱን ለማውጣት ቀጠሮ በተያዘበት ዋዜማ ነበር።
ስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ እና ተቃዋሚው እጩ ፈርናንዶ ዲያስ ዳ ኮስታ ሁለቱም አሸንፈናል ብለው ነበር።
በዚሁ ዕለት ወታደሩ ስልጣን የተቆጣጠረ ሲሆን፤ ኤምባሎ ይህንን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲሉ ገልጸውታል።
መኮንኖቹ የቀድሞውን የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሆርታ ኢንታ-አን በሀገሪቱ መሪነት ሾመዋል። ስልጣኑ በተያዘ በማግስቱም በይፋ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በሌላ በኩል፤ ኤምባሎ ወደ ሴኔጋል ከሸሹ በኋላ ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ መዲና ብራዛቪል አምርተዋል።
የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና የጊኒ ቢሳው ተቃዋሚዎች ኤምባሎ እና በወታደሩ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎቻቸው ይህንን መፈንቅለ መንግስት ያቀነባበሩት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሊደርስባቸው የሚችለውን ሽንፈት ለማስቀረት ነው ሲሉ ከሰዋል እንደ አፍሪካ ኒዉስ ዘገባ።
እስከዳር ግርማ
ህዳር 24/2018 ዓ.ም
