በአማራ ክልል ጎብኚዎችን መቀበል የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ቢገኙም የሰለጠነ የሰው ሀይል ክፍተት ግን እንዳለባቸው የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል ።
በአማራ ክልል በ2018 የመጀመሪያ ሩብ አመት 11 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ታቅዶ 5ሺህ 46 ጎብኚዎች ማስተናገድ መቻሉን የክልሉ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
እንዲሁም ከ6 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ይመጣል ተብሎ እቅድ ተይዞ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቱሪስት ክልሉን መጎብኘታቸውን አንስተዋል ።
በቀጣይ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚፈጥሩ በዓላት ስለሚከበሩ ቁጥሩ የበለጠ ሊጨምር እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የውጭ ሀገር ቱሪስት ላሊበላን ሳይጎበኝ እንደማይመለሱ ጥናቶች እንደሚያሳዩ እና በህዳር ወር ብቻ ከ 1ሺ በላይ ቱሪስቶች እንደጎበኙት ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን የቱሪስት ፍሰት ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እና የቅርስ ጥገናዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አቶ መልካሙ ገልፀዋል።
ሐመረ ፍሬው
ህዳር 29/2018 ዓ.ም
